D
Posted by Diredawa Prosperity Party
Jul 05, 2026 11 views 0 Comments
"የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ ማረጋገጥ ይገባል።"
‎ወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ
‎የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ የሴቶች ክንፍ ሀላፊ
#DIREPROSPERITY | ሰኔ 26/2018
‎የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሴቶች ክንፍ ፅ/ቤት የ2018 እቅድ አፈፃፀም፣ የ2019 እቅድ እንዲሁም የክረምት በጎ ፈቃድ ማቀጣጠያ መድረክ አካሄደ።
‎ብልፅግና ፓርቲ የሀገራችንን ሴቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ትርጉም ባለው መልኩ ለማረጋገጥ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሴቶች ክንፍ ፅ/ቤት ሀላፊ ወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ ሲሉ መድረኩን በይፋ በከፈቱበት ወቅት ተናግረዋል።
‎የሴቶች ንፅህና መጠበቂያን በመደገፍ በትምህርት ቤት የሚገኙ ሴት ተማሪዎች ሲገጥማቸው የነበሩ ችግሮችን በመቅረፍ በትምህርታቸው ውጤታማ ማድረግ ይገባል ያሉት ሀላፊዋ ወ/ሮ ሁክሚያ መሀመድ በቀጣይ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በአስተዳደሩ ከተማና ገጠር የሚገኙ የኢኮኖሚ አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ሴት ተማሪዎች ድጋፍ ይደረጋል ብለዋል።
‎በ2018 በጀት ዓመት በሴክተር፣ ወረዳና ክላስተር የሚገኙ የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ሴቶች ክንፍ አደረጃጀቶችን በዋናነት የህብረትና የቤተሰብ አባላቶችን የማጥራት ስራ መሰራቱን የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ሴቶች ክንፍ ፅ/ቤት የአደረጃጀት ዘርፍ ሀላፊ ወ/ሮ አይናለም መንገሻ በመድረክ ባቀረቡት የፅ/ቤታቸው ሪፖርት ጠቁመው አባላትን በአዲስ መልኩ የመመልመል ስራም በትኩረት መሰራቱን አክለው ገልፀዋል።
‎7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በአስተዳደር ደረጃ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ በሆነ መልኩ በፓርቲያችን አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ የሴቶች ክንፍ አመራሮችና አባላት የአንበሳውን ድርሻ መወጣት የቻሉበት ውጤታማ ስራ መሰራቱን ወ/ሮ አይናለም መንገሻ ተናግረዋል።
‎ሴቶችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከማድረግ አንፃር እንዲሁም በስራ እድል ፈጠራ ከሚመለከታቸው ሴክተር ተቋማት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራ መስራት ተችሏል።
‎ሴቶች በትምህርትና በጤና ማህበራዊ ዘርፍ አገልግሎቶች በተለይም በጤና መድህን ዋስትና ተጠቃሚ በማድረግ የሴቶችን ኑሮ ማሻሻል መቻሉም ተገልጿል።
‎በመድረኩ ላይ የአስተዳደሩ ሴክተር ተቋማት፣ የከተማ ወረዳና የገጠር ክላስተሮች የ2018 እቅድ አፈፃፀም በዝርዝር አቅርበዋል።
‎የአባላት ገቢ አሰባሰብ፣ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ፣ አምስት ሚሊየን ኮደርስ፣ የአቅም ግንባታ ስልጠና፣ ምሁራንን መሰረት ያደረገ አዳዲስ ወጣት ሴት አባላቶችን መመልመል እና ሌሎች መሰል ስራዎች በበጀት ዓመቱ የተከናወኑ አበይት ተግባራት ናቸው።
‎በመጨረሻም የብልፅግና ፓርቲ ድሬዳዋ ቅርንጫፍ ሴቶች ክንፍ ፅ/ቤት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት እቅድ የቀረበ ሲሆን ተሳታፊዎችም በመድረክ በቀረበው የ2018 አፈፃፀምና የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እቅድ ላይ ሀሳብና አስተያየት ሰጥተው ከመድረክ አወያየዮች ተገቢው ምላሽ ተሰጥቶበት የዕለቱ መድረክ ተጠናቋል።

 

#Badhaadhina

Comments (0)

Be the first to share your thoughts.

Leave a Comment

Your email will not be published. Required fields are marked *